ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ | Commissioner Tesfaye Debiso

ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ


 የሲዳማ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ


                   📢 መልዕክት

ፖሊስ የሌሎች ግለሰቦች ወይንም የወል ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ አገር፣ መንግሥት፣ መሥሪያ ቤቶች የመሳሰሉት ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደረስ ይከላከላል፤ ጉዳት ሲደርስም የጉዳት አድራሹን ማንነትና የድርጊቱን አፈጻጸም የሚያሳይ ማስረጃ ያፈላልጋል፤ ወይንም የወንጀል ምርመራ ያደርጋል፡፡ ፖሊስ እንደ ተቋምም በዋናነት ሁለት ተልዕኮዎች ያሉት ሲሆን እነዚህም ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት መከላከልና ከተፈፀመ በኋላ ምርመራ ማካሄድ ናቸው፡፡

ፖሊስ መደበኛ ስራዎችን በሚያከናውንበት ወቅት በሚወስዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጋለጡ ስለሆነ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይከሰቱ የፖሊስ አባላት ወደ ስራ ሲገቡ የተለያዩ የምልመላ መስፈርቶችን በማለፍ ነው፡፡ የፖሊስ ምልመላ መሥፈርት በዋናነት እንደመነሻ የሚነሳ ጉዳይ ያደርገዋል፡፡

በሃገራችንም ቢሆን ፖሊስ ለመሆን ፍላጎት ያለዉ ማንኛዉም ሰዉ፤ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ለፌዴራልና ለክልሎች ሕገ-መንግስት ታማኝና ተገዥ የሆነ፣ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት የሚያምን፣ በሃይማኖቶች እኩልነት የሚያምን፣ መልካም ሥነ-ምግባር ያለው፣ ዕድሜዉ ከ18 ዓመት ያላነሰ እና ከ25 ዓመት ያልበለጠ፣ የማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ፣ ለፖሊስነት የሚያበቃ አካላዊ ብቃትና የተሟላ ጤንነት ያለው፣ የወንጀል ቅጣት ሪከርድ የሌለበት እና የሚሰጡትን የመግቢያ ፈተናዎች ያለፈ መሆን እንዳለበት የኢፌዴሪ ፌዴራል ፖሊስ መተዳደሪያ ደምብ መረጃ ያሳያል።

በወንጀል በመከላከልም ይሁን በምርመራ ወቅት የሰብዓዊ መብትን እንዳይጥሱ በየጊዜው በቂ ሥልጠና ቢሰጥ መልካም እንደሆነ መረዳት ይቻላል። እንደ ሌሎች ሙያዎችም የፖሊስ የሥነ ምግባር ደንቦችም አሉ፡፡ በርካታ አገሮች የሥነ ምግባር ደንቦቹ በትክክል መተግበራቸውን የሚከታተል በፖሊስ ተቋሙ ውስጥም ሆነ ውጭ የሚገኙ ተቋማትና የተዘረጉ የአሠራር ስርዓቶችን ክትትል ማድረግ እና ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫ ማሳየትም ያስፈልጋል፡፡

ምክኒያቱም አንድ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ዳኛ ወይም ሌላ ባለሙያ የሙያውን ሥነ-ምግባር የሚተላለፍ አድራጎት ከፈፀመ ተጠያቂነት እንዳለበት ሁሉ ፖሊስም በወንጀል፣ በዲስፕሊንና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂና ኃላፊነት ሊኖርበት ስለሚገባ ይኼው አካሄድ እየዳበረ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የክልላችን ህዝቦች መሠረታዊ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ የሆነው በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ የመገንባት ዓላማ ከግብ የሚደርሰው የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበራቸው ሲረጋገጥ ነው። የፖሊስ ኮሚሽኑ ከህዝብ ጋር በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት በጥናትና ምርምር፣ ትንተና እና ከህዝብ አስተያየት በመነሳት ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን በማምከን የቅድመ መከላከል ስራ መስራት ይኖርበታል።

ከዚህ አልፎ ወንጀል ከተፈፀመ የወንጀል ድርጊቱን በማጣራት ማስረጃ በማሰባሰብ በጥፋተኞች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከአቃቤ ህግ አካላት ጋር በመተባበር እስከ መጨረሻው ጉዳዩን በመከታተል ፍርድ እንዲሰጥ ማድረግ ይኖርበታል።

በህዝቦች ትግልና ግፊት የመጣው ለውጥ ሀገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር፣ ለክልላችን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና መሠረት የሚጥል፣ የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እና ህዝቦች በኮሚሽኑ ላይ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በመፍታት እና የማይቋረጥ ቋሚ የአሰራር ሥርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ህዝቡን በታማኝነት መገልገል ይገባል።

በቅርብ ጊዜ ጀምሮ የክልላችን መንግሥት የፖሊስ አገልግሎት ተደራሽነት እና ብቃት ለማሳደግ አስፈላጊ እርምጃዎችን ወስዶ ዘመናዊ የፖሊስ አደረጃጀት ለመገንባት እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የፖሊስ ቁልፍ ሚና የወንጀል ተግባር በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዳይፈፀም መከላከል ነው፡፡

በፖሊስ ሥነ ምግባር ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊው ጉዳይ “መልካም እና ሃቀኛ ምግባር” መላበስ ነው። በመሆኑ የክልላችን ፖሊስ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ውስጣዊ ጥንካሬውን ፈትሾ ማሻሻያ የማድረግና የአገልግሎት አሰጣጥን ዲጅታል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ለመግለፅ እወደላለሁ። አመሰግናለሁ።

ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ | ዋና አዛዥ